Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሳዑዲ ጋር እንደምትሰራ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ እና በሪያድ መካከል የሚደረጉ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውሮችን ለመከላከል ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገለፀች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር ) ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የሀገራቱን የኢኮኖሚ ዘርፍ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ መክረዋል።

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በወቅቱ÷ በሱዳን ግጭት ዙሪያ ኢትዮጵያ ገለልተኛ አቋም እንደምታራምድ አስረድተዋል።

እንደ ጎረቤት እና ወዳጅ ሀገር በሱዳን የተፈጠረው ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንደምታግዝ አረጋግጠዋል።

ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ በበኩላቸው÷ ሪያድ የሱዳን ቀውስ መቋጫ እንዲያገኝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሳዑዲው አቻቸው ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል የኢኮኖሚ ትሰስር በሚጠናከርበት መንገድ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በውይቱይ አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመፍጠሩ የሳዑዲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል።

ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና ዘርፍ፣ በማዕድን፣ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የኢትዮጵያ መንግሥት የደኀንነት ስጋት አድርጎ እንደሚወስደው የጠቀሱት አምባሳደር ምስጋኑ፤ አደጋውን ለመከላከል ከሪያድ ጋር ጠንካራ ትብብር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.