Fana: At a Speed of Life!

ፋና ላምሮት የምዕራፍ 19 የፍጻሜ ውድድር ነገ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሶስት ወራት በጠንካራ ፉክክር ሲካሄድ የቆየው ፋና ላምሮት የምዕራፍ 19 የፍጻሜ ውድድር ነገ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል።

ለፍፃሜ የደረሱት አራቱ ተወዳዳሪዎች ብሩክ ሰለሞን፣ ዮሴፍ ጉልላት፣ ካሳሁን ዘውዱ እና ኤፍሬም ጌታቸው በነገው እለት ብርቱ ፉክክር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።

ተወዳዳሪዎቹ በሶስት ዙር የመረጧቸውን ሙዚቃዎች ከኮከብ ባንድ ጋር የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለተወዳዳሪዎቹ የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት አዘጋጅቷል።

ለ5ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በቀጥታ ማለፋቸውን ባለፈው ሳምንት ያረጋገጡት ተወዳዳሪዎቹ፤ 1ኛ ደረጃን የሚያገኝ 400 ሺህ ብር፣ 2ኛ ደረጃ 300 ሺህ ብር፣ 3ኛ ደረጃ 200 ሺህ ብር እንዲሁም 4ኛ ደረጃን የሚያገኝ 100 ሺህ ብር ሽልማት ይበረከትለታል።

በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሚካሄደው የፍፃሜ ውድድር ላይ አንድ ተወዳጅ ድምፃዊ በክብር እንግድነት ይገኛል።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንም አድማጭ ተመልካቾቹን የፍፃሜ ውድድር በሁለቱም የፋና ቴሌቪዥን ቻናሎች፣ በፋና ኤፍኤም 98 ነጥብ 1 እና በክልል ኤፍኤሞች፣ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች በቀጥታ እንዲከታተሉ ጋብዟል።

ነገ ቅዳሜ ከ6:00 ጀምሮ ውድድሩን በመከታተል በዕለቱ የሚገለፀውን የተወዳዳሪዎችን ኮድ በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ እየተዝናናችሁ እንድትደግፉ ይጋብዛል።

በለምለም ዮሐንስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.