Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለኮሪያ ነጻነት የከፈለችው መስዋዕትነት ለሀገራቱ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ነው  – አምባሳደር ጁንግ ካንግ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነጻነት የከፈለችው መስዋዕትነት ለዘመናት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ገለጹ።

74ኛው የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ክብረ በዓል በኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል።

አምባሳደር ጁንግ ካንግ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ ከ74 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኮሪያ ሰላምና ነጻነት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

የተከፈለው መስዋዕትነት ኮሪያ ሪፐብሊክ ወደ ነበረችበት ሰላምና ደህንነት እንድትመለስ ከማድረግ ባለፈ አሁን ለደረሰችበት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በኮሪያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለነበራት ተሳትፎ የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስትና ሕዝብ ትልቅ ክብርና ምስጋና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በታሪክና በመስዋዕትነት የተሳሰረውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር  ሀገራቱ በባህል፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና መሰል ሥራዎች ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ለማጠናከር በትብብር የሚከናወኑ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማህበር ሊቀ መንበር ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነጻነትና ሰላም የከፈለችው መስዋዕትነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የሚኖር አኩሪ ታሪክ ነው።

በጀግኖች አባቶቻችን የተጻፈው ደማቅ ታሪክ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያላትን ተደማጭነትና ተፈላጊነት ያጎለበት መሆኑ ጠቅሰው÷ ተልዕኮው የኮሪያ ሪፐብሊክን ሰላም ከማስጠበቅ በዘለለ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱ ትውልድ ቀደምት አባቶች በመስዋዕትነት ያስረከቡትን ሀገር ሰላሟን ከማስጠበቅ ባሻገር ልማቷን ማፋጠን ይጠበቅበታል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.