Fana: At a Speed of Life!

የበልግ ወቅት የመጨረሻ ወር የዝናብ ስርጭትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚዋዥቅ እና ተለዋዋጭ እየሆነ የመጣውን የበልግ ወቅት የመጨረሻ ጊዜያት የዝናብ ስርጭት በአግባቡ በመሰብሰብ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በኢንስቲትዩቱ የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለፋና ዲጅታል እንደገለጹት፤ ባለፉት ሦስት ወራት የበልግ ዝናብ በሚያገኙ የሀገራችን ክፍሎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የሆኑ የዝናብ መጠን እና ስርጭት ነበራቸው።

ከዓመታዊ የዝናብ ስርጭት 55 በመቶውን በበልግ ወቅት የሚያገኙት የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል፣ የጉጂ እና የቦረና ዞኖች፣ የሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነባቸው አካባቢዎች እስከ 350 ሚ.ሜ የዝናብ መጠን መመዝገቡን ገልጸዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት የነበረው የዝናብ መጠን እና ስርጭት ለበልግ የግብርና ስራዎች፣ ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውሃ እንዲሁም ለእንስሳት መኖ አቅርቦት እጅግ ትልቅ ጠቀሜታ ነበረው ብለዋል።

ለበልግ ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታ እንዳለ እና በ24 ሰዓታት ውስጥ 126 በሚደርሱ አካባቢዎች ከ30 እስከ 102 ሚ.ሜ የሚደርስ እጅግ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ መመዝገቡን አብራርተዋል።

በቀሪው የበልግ ወቅት የግንቦት ወር በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ የደመና ሽፋን እንደሚኖር ጠቅሰው፤ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች፣ በደቡብ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች፣ በሲዳማ ክልል እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠን እና ስርጭት እንደሚኖር ጠቁመዋል።

የሚኖረው የዝናብ መጠን የግብርና እንቅስቃሴዎችን ለመከወን፣ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ለመስራት፣ የተፋሰሶች ውሃ የመያዝ አቅም እንዲሻሻል በማድረግ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የበልግ ወቅት የዝናብ መጠን እና ስርጭት የመዋዠቅ እና ከቦታ ቦታ ተለዋዋጭነቱ ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ የሚኖረውን የዝናብ ስርጭት በአግባቡ በመሰብሰብ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ማህበረሰቡ አካባቢውን የማጽዳት እና የታቆሩ ውሃዎችን የማፋሰስ ተግባር ማከናወን እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.