ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጉልህ ስኬቶች ተመዝግበዋል – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ጉልህ ስኬቶች መመዝገባቸውን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ ÷ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሸን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።
በመክፈቻ ንግግራቸውም ባለፉት ዓመታት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው ÷ ይህም ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርጾ በመተግበርም የዲጂታል ምህዳርን እና የወጣቶችን የፈጠራ ባህልን ማጎልበት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን አቅም ለመገንባት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተለዋዋጩን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ሁለንተናዊ ደህንነትንና የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጓ የፋይናንስ ሥርዓቱን ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉን አንስተዋል።
በኤክስፖው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያተረፉ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ተመላክቷል፡፡