የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሕዝቦችን አንድነት በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፉ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሕዝቦችን ሰላም እና አንድነት በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡
“ጥበብና ሀገር፣ ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት”በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የውይይት መድረክ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተካሄደ ነው፡፡
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሃላፊ ሐይማኖት አለማየሁ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል፡፡
ለዚህም የኪነ ጥበብ ዘርፉን አቅም በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን መከወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተካሄደ በሚገኘው የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ውይይት ÷መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ የተለያዩ የሕዝብ መዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን፣ ተርሚናሎችን፣ ፖርኮችን፣ የንግድ ዘርፎችን ያቀፉ ተቋማትን፣ ታሪካዊ ቅርሶችን እና ሌሎች ሰው ተኮር ልማቶችን ጎብኝተዋል፡፡
በዚህ ወቅም ከተማ አስተዳደሩ ባከናወናቸው ሰው ተኮር ሥራዎች መደሰታቸውን ገልጸው÷መንግስት የሚያከናውናቸውን የልማት ሥራዎች በሙያቸው ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በተመሳሳይ በሀገራዊ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መድረክ በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች ከሚገኙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
መድረኩ በዋናነት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በልማት ሥራዎች እንዲሳተፉ ለማድረግ እንዲሁም የሕዝብን ሰላም እና አንድነት በሚያጠናከሩ ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሀገራዊ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች የውይይት መድረክ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ