የባህላዊ ግጭት አፈታት ሂደቶችን ሚና በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህላዊ ግጭት አፈታት ሂደቶችን ሚና በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪስ አስገነዘቡ።
2ኛዉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና የጋምቤላ ክልሎች የሰላም እና የልማት ትብብር ፎረም በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በፎረሙ ላይ የተገኙት ሚኒስትሩ÷ በተፈጥሮ ሀብት የታደሉት ሁለቱ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች ያላቸውን ሀብት በሚፈለገው ልክ አልምተው መጠቀም እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ለዚህ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሂደቶች ያላቸውን ሚና በማጎልበት በአዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሠላምን እና ልማትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ በሁለቱ አዋሳኝ ክልሎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ ለመከላከልና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተመሠረተዉ ፎረም አበረታች ዉጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
የሁለቱ ክልሎች ህዝብ የጋራ ዓላማ እና ራዕይ አለው በማለት ገልጸው÷ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እነዚህን የጸጥታ ችግሮች በተደራጀ መንገድ መከላከል፣ አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ እና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል ነዉ ያሉት።
የሁለቱ ክልሎች ህዝብ ያለው የእርስ በርስ ግንኙነት እና ማህበራዊ መስተጋብር ዘመናት የተሻገረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ናቸው።
የግል አጀንዳ ያላቸዉ ግለሰቦች ግጭት በመፍጠር የህዝቦችን አብሮነት ለመሸርሸር ሙከራ ሲያደርጉ መቆየታቸዉን ጠቅሰው÷ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በየጊዜዉ መወያየት እና የልማት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዘላለም ግድየለው