በአዲስ ገጽታ እንግዶቿን በመቀበል ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በገበታ ለሸገር መርሐ ግብር በተገነቡት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማት ስራዎች አዲስ ገጽታ ተላብሳለች፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተተገበረው ߵߵገበታ ለሸገርߴߴ አማካኝነት ከተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የአንድነት እና እንጦጦ ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይና የወንዝ ዳር ልማቶች ይጠቀሳሉ፡፡
መዲናዋ በእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማት ስራዎች አዲስ ገጽታ በመላበስ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊ እንግዶቿን በመቀበል ላይ ትገኛለች፡፡
እነዚህ መዳረሻዎች ከተማዋ ለዘመናት የነበራትን መልክ በልዩ ሁኔታ በመቀየር ለዓይን ማራኪና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን አስችለዋታል።
በተጨማሪም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ከፍ ከማድረጋቸው ባሻገር የአፍሪካ መሪዎችና ዓለም አቀፍ ልዑካን በጉባኤዎች ወቅት የሚዝናኑባቸውና የሀገሪቱን ብዝሃነት የሚረዱባቸው የኩራት ተምሳሌቶች ሆነዋል።
እነዚህ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ከመደበኛው የጉባኤ አጀንዳ ጎን ለጎን ለሚካሄዱ የጎንዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች አመቺ መድረክ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
መሪዎችና ዲፕሎማቶች ከስብሰባ አዳራሾች ወጣ በማለት በተፈጥሮና በታሪክ የታጀቡ ስፍራዎች ላይ መንፈስን በሚያድስ ከባቢ እንዲወያዩ ዕድል መፈጠሩ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ አዲስ ጉልበት ይሰጣል።
በተለይም በፓርኮቹ ውስጥ የሚታዩት የታሪክ አሻራዎች አፍሪካውያን እንግዶች የጋራ ማንነታቸውንና የነጻነት ትግላቸውን የሚያስታውሱ መሆናቸው አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም ያላትን ሚና ከፍ ያደርጋሉ፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የጉባኤ ተሳታፊዎችና ጋዜጠኞች በእነዚህ መዳረሻዎች ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ መደረጉ ለሆቴል ኢንዱስትሪው፣ ለትራንስፖርት ዘርፉና ለሀገር በቀል የእደጥበብ ውጤቶች ሰፊ የገበያ ዕድል በመፍጠር የከተማዋ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ አድርጓል፡፡
ይህ የቱሪዝም ፍሰት መጨመር የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም ባሻገር አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና የቱሪዝም መዳረሻ ሆና እንድትቀጥል የሚያስችል ስትራቴጂያዊ አቅም መገንባቷን ያሳያል።