ሌብነት ስብራት እንደሆነ ወስደን በሦስት ምዕራፍ ከፍለን ለመከላከል እየሰራን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብሔራዊ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰው ሌብነት አንዱ ስብራት እንደሆነ ወስደን በሦስት ምዕራፍ ከፍለን ለመከላከል እየሰራን እንገኛለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ባለ አራት ክፍል ቃለ ምልልስ በክፍል አራት የገንዘብ፣ የጊዜ፣ የቸልተኝነት ሌብነት እሴት፣ ሞራል እና እምነት የሸረሸረ፤ በመትጋት ያለች ሀገር ውስጥ እንቅፋት እና አደገኛ ስብራት መሆኑን ገልጸዋል።
በብሔራዊ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰው ሌብነት አንዱ ስብራት እንደሆነ ወስደን በሦስት ምዕራፍ ከፍለን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ መንግስታዊ ወይም ተቋማዊ ሌብነትን ማስቆም እንደሆነ ጠቅሰው፥ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስታዊ ሌብነት የለም ብለዋል።
መንግሥታዊ ሌብነት የለም ማለት በግለሰብ ደረጃ ሌባ ባለስልጣን የለም ማለት አለመሆኑን አስረድተዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በጊዜ ሂደት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል እና ህዝብን የሚያማርረው ትንንሽ ሙስናና ሌብነትን መቀነስ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሄንን ለመፍታት ዋነኛ አማራጩ ሌብነት እንዳይኖር የሚያደርግ ስርዓት መዘርጋት እንደሆነ ገልጸው፥ ለዚህም አንዱ ማሳያ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ለድርድር እና ለሌብነት የማይመች እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህን አይነት ስርዓትን በመዘርጋት ሌብነት መቀነስ እንደሚቻል አብራርተዋል።
እንዲሁም ሌብነት የሚጠየፍ ባህልን መገንባት ሦስትኛው ምዕራፍ እንደሆነ አንስተው፥ ይህም ሰፊ ጊዜን የሚወስድ እና የትርክት ውጤት እያደገ ሲሄድ የሚመጣ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
በመሆኑም ሌብነትን ስርዓትና ትርክት እየገነባን ስናጠፋው ለኢትዮጵያ እድገት እና ብልጽግና እጂግ ጠቃሚ እንደሆን አመልክተዋል።
በዮናስ ጌትነት