Fana: At a Speed of Life!

ተወዳዳሪ ዜጋ እንድትሆኑ ሳትሰርቁ ጠንክራችሁ ፈተናችሁን በራሳችሁ ሥሩ – ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በከምባታ ዞን ሺንሺቾ አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የ6ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና መርሐ ግብርን አስጀምረዋል።

በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክል ርዕሰ መስተዳድር፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ከስርቆት እና ከማጭበርበር በጸዳ መልኩ ጠንክራችሁ ፈተናችሁን ሥሩ በማለት ለተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተማሪዎች በራሳቸው የመተማመን አቅማቸውን በማሳደግ ተወዳዳሪ ዜጋ ሆነው በሀገሪቱ እድገት ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ እንዲችሉም ሚኒስትሩ አበረታተዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ በሺንሺቾ ከተማ በብራይት ቪዥን ቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ለህጻናት እየተሰጠ ያለውን ትምህርት ምልከታ አድርገዋል።

አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሰጠው የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 98 ሺህ 107 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ፖሊሲ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ የምዘና ስርዓት በመቀየሩ የተማሪዎችን ክህሎት በማሳደግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.