በፖሊዮ ክትባት ዘመቻው እስካሁን 15 ነጥብ 3 ሚሊየን ሕጻናት ተከትበዋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እስካሁን 15 ነጥብ 3 ሚሊየን ሕጻናት ተከትበዋል አለ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፡፡
በኢንስቲትዩቱ የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት ÷ የፖሊዮ ወረርሽኝን ለማጥፋት የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
በዚህ መሰረትም የፖሊዮ ወረርሽኝ የቅኝት ሥራዎችን ከማከናወን ባለፈ የተቀናጀ የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡
2ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ÷ በዚህም እስካሁን 15 ነጥብ 3 ሚሊየን ሕጻናት መከተባቸውን ተናግረዋል፡፡
ክትባቱን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ፖሊዮን ለማጥፋት ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጹት አስተባባሪው÷ በቀጣይ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
የክትባት ዘመቻውን የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን