Fana: At a Speed of Life!

“የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን ሕይወት ይቀይራል” አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል አሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በ2018 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገውን የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ÷ በኮሪደር ልማት ሥራ ከተሞችን የተሻለ ገጽታ ማላበስ እየተቻለ ነው፡፡

በተለይም ከተሞች በሥርዓት የሚመሩ ውብና ጽዱ እንዲሆኑ በማስቻል ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን የፈጠረ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በሐረር ከተማም በኮሪደር ልማት አበረታች ውጤት መገኘቱን ጠቁመው ÷ በቀጣይ 2018 ለገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ትኩረቱ በመስጠት በከተማ የተመዘገበውን ውጤት በገጠሩ ክፍል ለማስፋት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

በገጠር አካባቢ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘዬ መቀየር እንደሚያስችሉ  አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለአብነትም አርሶ አደሩ ያለውን ሃብትና ፀጋ በአግባቡ ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን በማሳደግ በዚያው ልክ ሕይወቱን እንዲመራ በማስቻል በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል  ያግዛል ነው ያሉት፡፡

በገጠር እና በከተማ መካከል ያለውን የአኗኗር ዘዬ ልዩነት በማጥበብ ማሕበረሰቡ በቀላሉ የሚገናኝበትን ዕድል በመፍጠር ጠንካራ ማሕበራዊ ትስስር እንዲፈጠር ያስችላልም ብለዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎች ስኬታማነት ትኩረት በመስጠት የተያዘው እቅድ ተፈጻሚ እንዲሆን ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በተስፋዬ ሃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.