የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና እየወሰዱ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት 299 ሺህ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና እየወሰዱ ነው አለ፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ፈተናውን እየወሰዱ ከሚገኙት ተማሪዎች መካከል 31 ሺህ 50 የሚሆኑት በበይነ መረብ እየተፈተኑ ነው።
በበይነ መረብ የሚፈተኑት ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያ እንዳይቸገሩ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡
በሁሉም የመፈተኛ ማዕከላት የመብራት እና ኢንተርኔት መቆራረጥ እንዲሁም የሰው ኃይል እጥረት ሳያጋጥመን ፈተናውን እየሰጠን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ፈተናው በሰላማዊ መንገድ እየሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ ያልተፈቀዱ ነገሮችን ፍተሻ አልፈው በመፈተኛ ክፍል ውስጥ ይዘው የተገኙ ተፈታኞች ከፈተና መሰረዛቸውን አብራርተዋል፡፡
የመጀመሪያ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓም ድረስ ይሰጣል፡፡
ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከሐምሌ 4 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓም እንደሚሰጥ ገልፀው፤ በሁለተኛው ዙር ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች በበይነ መረብ ብቻ የሚፈተኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ