ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የጋራ ጥረት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰው የመነገድና በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል አለ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ፡፡
ቢሮው በሰው የመነገድ፥ በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገርና ተያያዥ ወንጀሎችን ለመከላከል የተቋቋሙ ክልላዊ የትብብርና ጥምረት አደረጃጀቶችን አቅም ለማጠናከር ያለመ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የፍትህ ቢሮ ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ጎሽም በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ፣ ወንጀሎችን ለመከላከል የተቋቋሙ ጥምረቶች ደካማ መሆንና ሕግ የማስከበር አቅም አነስኛ መሆን ወንጀሎችን እንዳይቀንሱ አድርጓል።
የዜጎችን ደህነንት እንዲሁም የሀገርን መልካም ስምና ክብር ለማስጠበቅ መሥራት የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ወንጀሉን የመቆጣጠር አቅምን ለማሳደግ አደረጃጀቶችን ማጠናከርና ከባለድርሻ አካላት ጋር ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶችን ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአጋር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበር ፕሬዚዳንት አበራ አደባ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ጤንነቱ የተጠበቀ፣ ሀገር ወዳድና በሀገሩ ሥራ ፈጥሮና ሰርቶ መለወጥ የሚችል ማኅበረሰብ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዋነኛው ምክንያት ድህነት እና ስራ አጥነት መሆኑን ገልጸው÷ ትውልዱ በሀገሩ ሰርቶ መለወጥ እንደሚችል ማሳየት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ