Fana: At a Speed of Life!

ሌዋንዶውስኪ ማንቼስተር ዩናይትድን ለመቀላቀል ተቃርቦ እንደነበር ተናገረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፖላንዳዊው የባርሴሎና አጥቂ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ በአንድ ወቅት ማንቼስተር ዩናይትድን ለመቀላቀል ተቃርቦ እንደነበር ተናገረ፡፡

የ37 አመቱ አጥቂ ከበቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በፈረንጆቹ 2012 ማንቼስተር ዩናይትድን ለመቀላቀል ፍላጎት እንደነበረውና ዩናይትድ እሺታውን ገልጾ እንደነበር አስታውሷል፡፡

ለስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ባለው አድናቆት ዩናይትድን መቀላቀል ቢፈልግም ክለቡ ቦሩሺያ ዶርትመንድ የተሻለ የዝውውር ገንዘብ ለማግኘት በማሰቡ ዝውውሩ እንደተደናቀፈ ተናግሯል፡፡

ተጫዋቹ ለአውሮፓ ትላልቆቹ ክለቦች ማለትም ባየርን ሙኒክ እና ባርሴሎና በመጫወት ቻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ የቡንደስ ሊጋ እና የላሊጋ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡

በ37 አመቱ እግር ኳስን የማቆም ፍላጎትና እቅድ እንደሌለው የሚገልጸው ሌዋንዶውስኪ፥ ስኬታማ የእግር ኳስ ህይወት ቢያሳልፍም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አለመጫወቱ እንደሚቆጨው ተናግሯል፡፡

በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነት ባሳለፋቸው 21 ዓመታት 700 ግቦችን ለሀገሩና ለተጫወታባቸው ክለቦች ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፥ ለመጪው የ2025/26 የወድድር ዘመን ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

የባሎንዶር ሽልማትን ማሸነፍ ከሚገባቸው ተጫዋቾች መካከል ስሙ የሚነሳው ተጫዋቹ፥ በፈረንጆቹ 2020 የባሎንዶር አሸናፊነት ቅድመ ግምት ቢሰጠውም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሽልማቱ መሰረዙ ይታወሳል፡፡

በእግር ኳስ ህይወቱ በታላላቅ አሰልጣኞች የመሰልጠን እድል ያገኘው ሌዋንዶውስኪ፥ ለጀርመናዊው አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ የተለየ አድናቆትና ክብር እንዳለው ጠቅሷል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.