Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ) እንዳሉት፥ በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የት ቦታ እና ማን ጋር ምን አይነት ቅርስ ይገኛል የሚለውን የመለየት ስራ እየተሰራ ይገኛል።

ከሀገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ለተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንደማስረጃ የሚቀርበው ተለይቶ የተሰነደ ማስረጃ  ነው ብለዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ ጥረት በተለያዩ ግለሰቦች እጅ የሚገኙ ቅርሶችን ጨምሮ በርካታ ቅርስ በፈቃደኝነትና በድርድር ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቅርሶች በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለጨረታ ሲቀርቡ በህጋዊ መንገድ ከጨረታ እንዲወርዱ በማድረግ ለማስመለስ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

በዚህምበተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ፣ የራስ ደስታ ዳምጠው ካባ፣ የኢትዮጵያ ኮከብ ኒሻን እና ሌሎች ከጨረታው እንዲወርዱ በማድረግ ማስመለስ መቻሉን በአብነት ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሂደቱ የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸው፥ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ አዳዲስ የተፈጥሮ እና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም አልነጃሺ፣ ቡና፣ ዋዛ (በተለምዶ ዙምባራ የሚባለው)፣ አገው ፈረሰኛ፣ ሀላባ ሴራ፣ እንሰት እና መሰል ቅርሶችን ማስመዝገብ የሚያስችል የሰነድ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.