Fana: At a Speed of Life!

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን የመረዳዳት እሴቶች ተቋማዊ ያደርጋል – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴቶች ተቋማዊ የሚያደርግ ነው አሉ።

የክልሉ የዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ ተጀምሯል::

በመርሐ ግብሩ ላይ ክልላዊ የ4 ሺህ 600 አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና ዕድሳት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

አቶ ጥላሁን ከበደ በሥነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴቶች ተቋማዊ ያደርጋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚሸፈኑ ተግባራት ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት እንደሚቻል ገልጸው፤ አገልግሎቶቹ ሰው ተኮር በመሆናቸው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዓይነትም ሆነ በመጠን እየሰፋ በመምጣቱ ዜጎች ለአዎንታዊ ለውጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማ ዜጎችን ሕይወት እንደሚያሻሽል ጠቅሰው÷ በጎነት ለአብሮነት፤ ለሀገር ከፍታና ለራስ ስለሆነ በመርሃ ግብሩ በንቃት መሳተፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ባሉን  የተፈጥሮ ፀጋዎች ላይ በጎነትንና ቅንነትን በማከል እርስ በርስ ከተባበርን፤ ከተጋገዝንና ከተደመርን ጊዜያዊ ችግሮችን በመሻገር ባጠረ ጊዜ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.