ከሟች መቃብር ፊት ለይቅርታ የቆሙት ፖሊሶች…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ከሟች መቃብር ፊት አበባ ይዘው ለይቅርታ እጅ የነሱት ጃፓናውያን ፖሊሶች ጉዳይ ትኩረት የሳበ ክስተት ሆኗል፡፡
ጃፓናውያኑን ተንበርክከው ይቅርታን ለመማጸን ከሟች የመቃብር ስፍራ ድረስ ያመጣቸው ጉዳይ ከአምስት ዓመታት በፊት የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡
ሺዞ አይሽማ የተባለውን ጃፓናዊ ግለሰብ ጨምሮ ሌሎች ሶስት ሰዎች በፈረንጆቹ 2020 ምናልባትም ለወታደራዊ ግልጋሎት ሊውሉ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ማሽኖችን ወደ ውጭ ሀገራት በማስወጣት በፖሊስ ተከሰው ለእስር ይዳረጋሉ፡፡
በዚህ የክስ ሂደት ላይ ሳሉ ታዲያ ሺዞ አይሽማ ለእስር ከተዳረገ ከአንድ አመት በኋላ በጨጓራ ካንሰር ምክንያት ህይወት ያልፋል፡፡
የግለሰቡ ህይወት ካለፈ ከአምስት ወራት በኋላ ከቀረበበት ክስ ነጻ በመባል ክሱ ውድቅ መደረጉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡
ከዚህ በኋላ ታዲያ የአይሽማ ድርጅት በሀሰት ክስ ካሳ ይገባኛል በማለት ክስ ማቅረቡን ተከትሎ፥ የቶኪዮ ፍርድ ቤት ክሱ ህገወጥ ነበር በማለት የ166 ሚሊየን የን (1 ነጥብ 12 ሚሊየን ዶላር) ካሳ እንዲከፈላቸው ውሳኔ አሳልፏል፡፡
አይሽማ ስምንት ጊዜ ዋስትና እንዲከበርለት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፥ ሁሉም የዋስትና ጥያቄዎች ውድቅ ተደርገውበት እስከ ሞቱ ድረስ በእስር ቤት ለመቆየት ተገድዶ ነበር፡፡
ክሱን ይዘው የነበሩት ዐቃቤ ህግ፥ በህገ ወጥ መንገድ እንዲታሰሩ በመጠየቅና ክስ በመመስረት እንዲሁም ተከሳሹ ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የህክምና እድል በመንፈግ ለደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።
በዚህ ክስተት ማዘናቸውን የገለጹት የፖሊስ ባለስልጣናት የአበባ ጉንጉን ይዘው በሟቹ ሺዞ አይሽማ የመቃብር ስፍራ በመገኘት ይቅርታን ተማጽነዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለሰጠው የካሳ ብይንም ይግባኝ አለመጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ