ትውልዱ የዘመናት የልማት ቁጭቱን ያሳካበት የሕዳሴ ግድብ…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ትውልዱ በራሱ አቅምና በብርቱ ክንዱ የዘመናት የልማት ቁጭቱን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማሳካት ችሏል አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ።
ሚኒስትሩ እንዳሉት ÷ ግዙፉ የአፍሪካ ፕሮጀክት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ስኬት ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ደማቅ የልማት አሻራ ነው፡፡
በፕሮጀክቱ ግንባታ ሒደት በመላ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በንቃት በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ መጻፋቸውን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ፍትሐዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ሥርዓት እንዲሰፍን አበክራ ስትሰራ መቆየቷን ጠቅሰው ÷ የሕዳሴ ግድብ ስኬትም ለዘመናት የቆየውን ኢ ፍትሐዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም የሻረ ነው ብለዋል፡፡
የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት አስተማማኝ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ በማድረግ ሲያጋጥማቸው የነበረን የጎርፍ አደጋ ማስቀረት እንዳስቻለም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ግዙፉን የልማት ፕሮጀክት ያሳካችበትን መንገድ ከተፋሰሱና ቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚነት ባሻገር የአፍሪካ ሀገራት ልምድ ለመውሰድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው ያብራሩት፡፡
የሕዳሴ ግድብ የተሸከመው ውሃ ከኃይል አቅርቦት ደጀንነት ባሻገር የዓሳ ሃብት በረከት እና የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ እየሆነ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ሀገራዊና ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን ተደራሽነትን ለማስፋት ከፍተኛ አቅም መሆኑንም አስረድተዋል።