Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ አመት የኢትዮጵያን እምርታ ወደ ላቀ ደረጃ የምናሸጋግርበት ይሆናል – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ አመት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታችንን በማጎልበት የኢትዮጵያን እመርታ ወደ ላቀ ደረጃ የምናሸጋግርበት ይሆናል አሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፡፡

አፈ ጉባኤው አዲሱን አመት አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦች የላብና የደም አሻራ የሆነው ታላቁ  የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

አሮጌውን በአዲስ ለመተካት ፈተናዎችን በጽናት፣ በጥበብና በተስፋ መሻገርን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፥ ወደ ብልጽግና የሚያደርሰውን ጎዳና ለማደላደል በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ  መራመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በአዲሱ አመት የብልፅግና ጉዟችንን የሚያፋጥኑና ተወዳዳሪ ሊያደርጉን የሚችሉ የልማት ዕቅዶችን ተልመናል ያሉት አፈ ጉባኤው÷  የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በአሸናፊነት በመወጣት ለመጪዎቹ አመታት መሠረት ጥሎ ማለፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከልማት ጉዞ ባሻገር የዲሞክራሲ ባህል ግንባታን ማጎልበት፣ በክልሎች መካከል ፍትሐዊና ተመጣጣኝ እድገት እንዲኖር እንዲሁም ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዳይጣበብ ማድረግና የበይነ መንግሥታት ግንኙነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡

መንግሥታዊ ተቋማት፣ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ መገናኛ ብዙሃን እና መላው ህዝብ ለብልፅግና ጉዞ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.