ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከተመጽዋችነት መላቀቅ እንደምንችል ማሳያ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከተመጽዋችነት መላቀቅ እንደምንችል አመላካች ነው አሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ የግድቡን መጠናቀቅ በማስመልከት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ እንዳሉት፥ የግድቡ ዋና መልዕክት እንችላለን የሚል ነው፡፡
120 ሚሊየን ሕዝብ ተመጽዋች የሚለውን የመዘባበቻ ስም አሽቀንጥረን መጣል እንችላለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና መልዕክትም ይህ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በመልዕክታቸው፥ ኢትዮጵያውያን ሩቅ ያስባሉ፣ ይመራመራሉ፣ ይፈፅማሉ፣ ሰርተውም ያሳያሉ ነው ያሉት፡፡
የሁላችንም የእውቀትና የላብ ውጤት የሆነው ግድብ በመጠናቀቁ ደስታችንን በጋራ ለማክበር በመገናኘታችን እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፍጻሜውን እንዲያገኝ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡