Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የምግብ አምባሳደሯ ወይዘሮ ሙና በስኮትላንድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገረ ስኮትላንድ የሀበሻ ምግብ ቤት የከፈተችው ወይዘሮ ሙና የኢትጵያን ምግቦች በማስተዋወቅ ዝናን አትርፋለች፡፡

በራሷ ሼፍ ሙና የተመሰረተው ምግብ ቤቱ በሀገራችን በብዛት የተለመደውና የኢትዮጵያውያን መለያ የሆነው በየአይነቱ፣ ጥብስ፣ ክትፎ፣ ዶሮ ወጥ፣ ጥሬ ስጋ፣ ዱለት እና ሽሮ የመሳሰሉ ምግቦች የሚገኝበት ሬስቶራንት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ተጉዘው ወደ ስኮትላንድ ጎራ የሚሉ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም የኢትዮጵያን ምግብ የለመዱ የሀገሬው ስኮትላንዳውያንን ሞቅ ባለ መስተንግዶ ለዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ወይዘሮ ሙና ከምግብ ቤትና የንግድ ስራዎቿ ባለፈ የኢትዮጵያን ምግቦች በተመረጡ አደባባዮች ይዛ በመውጣት ማስተዋወቋ ደግሞ ሬስቶራንቷን በውጭ ሀገር ከተከፈቱ የሀበሻ ምግብ ቤቶች የተለየ ያደርገዋል፡፡

አንዳንዴ ምግቦችን በነፃ በማቅረብና በማስተዋወቅ እንዲሁም ምግቦች ላይ ልዩ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ የኢትዮጵያውያን ምግቦች በስኮትላንድ እንዲታወቁና እንዲለመዱ ማድረግ ችላለች፡፡

ብዙ ግዜ ምግቦቿን በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ይዛ በመውጣት እየተመገበች ሌሎችም እንዲመገቡ የምታደርገው የኢትዮጵያ ምግብ አምባሳደሯ ሼፍ ሙና መንገደኞች ምግቡን በነፃ በማቅመስ ታለማምዳለች፡፡

በዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውለደ አትዮጵያውያን እንዲሁም የስኮትላንድ ዜጎች ኢትዮጵያ እና ምግቦቿን እንዲያውቁ ማድረግ ችላለች፡፡

በዚህ ብቻ ሳታበቃ የኢትዮጵያውያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋ፣ ጭፈራ እና የአለባበስ ዘዴ በማስተዋወቅ ለሀገሯ የአምባሳደርነት ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡

ግለሰቧ የኢትዮጵያን ምግቦች ለማስተዋወቅ በምታደርገው ጥረትም በስኮትላንድ ባይት በተባለው ጋዜጣ እንዲሁም ኢድንበርግ በተባለው የስነ ምግብ ድረ ገፅ ላይ አርዕስት መሆን ችላለች፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.