በ”ዮ ማስቃላ” በዓል ላይ የሚካሄደው የ”ሶፌ” ሥነ ሥርዓት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋሞ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በሆነው በ”ዮ ማስቃላ” በዓል ላይ የሚካሄደው “ሶፌ” ሥነ ሥርዓት በብሔረሰቡ ዘንድ የሚከበር ደማቅ የበዓሉ ኹነት ነው፡፡
“ሶፌ” የሚለው ቃል ጋሞኛ ሲሆን÷ ሙሽሮች ቁንጅናቸውን በውድድር መልክ የሚያሳዩበት ባህላዊ ክዋኔ እና የ “ዮ ማስቃላ” በዓል እሴት ነው።
ሶፌ በዓመቱ ያገቡ ሙሽሮች የአከባቢው ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰቡበት ገበያ በመውጣት ዕውቅና ተሰጥቷቸው ከሕብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበት እንዲሁም የማን ቤተሰብ በደንብ ተንከባከበ፣ የማን ሚስት አማረባት በሚል ባልና የባል ቤተሰብ የሚገመገምበትና የሚዳኝበት ሥርዓት ነው።
የሶፌ ሥነ ሥርዓት በጋሞዎች ዘንድ የሚከበርና ከቦታ ቦታ የተወሰነ ለውጥ ያለው ሲሆን÷ አንዳንድ አካባቢ በፈረስ፣ አንዳንድ አካባቢ በእግር፣ አንዳንድ አካባቢ ደግሞ በርካታ ጨሌ በሙሽራዋ አንገት ላይ ይደረጋል።
በተመሳሳይ አንዳንድ አካባቢ ቅቤው በቅርጽ ተከምሮ ሲታይ በሌላ አካባቢ የሙሽራዋ ፀጉር በቅቤ ርሶ በብሔረሰቡ አጠራር “ፑንጽሮ” ይበጠራል፤ በአንዳንድ አካባቢ ካባ ይደረባል በአንዳንዱ አይደረግም።
ሶፌ በጋሞ ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ደረጃዎችን አልፎ መጨረሻ ላይ ሙሽሮች በባህላዊ መንገድ እንደተጋቡ ማሳወቂያ የባህል ሥርዓትም ነዉ፡፡
በጋሞ ባህል ያገባች ሙሽራ ከአንድ እስከ አራት ወር ከቤት ሳትወጣ የተለያዩ ሰውነት ገንቢ የሆኑ ለአብነትም ገንፎ፣ ቅንጬ፣ ጩኮ፣ ቡላ፣ በማር የታሸ ቆሎና የመሳሰሉ ምግቦችን እየተመገበች ትቆያለች።
በሙሽራውና ሙሽራዋ አብሮ አደጎች፣ ጎረቤት የተለያዩ ባህላዊ ሙዚቃ በክራር፣ ከበሮ፣ ዋሽንት እና ሌሎች መሳሪያዎች ታግዘው ባህላዊ ዜማዎችን እያዜሙ ይጨፍራሉ።
በሶፌ ዕለት በአከባቢው ሁሉም ያገቡ ሙሽሮች በወዳጅ ዘመድ ታጅበው በቅቤ የራሰውን ጸጉራቸውን ‘ፑንጽሮ’ አበጥረው፣ በከበረ ጨሌ፣ በጋሞዎች የጥበብ ቀሚስ አጊጠው፣ በጋቢ ተሸፋፍነው፣ በላዩ ላይ ሱፋሌ (ካባ) ደርበው፣ እንስራ ሙሉ ጠላ አስይዘው ወደ ገበያ ይወጡና ሴት ሙሽሮች ገበያውን አራት ጊዜ ይዞራሉ፡፡ ወንድ ሙሽሮች ደግሞ በተራቸው ሦስት ጊዜ ገበያውን ይዞራሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ጠላው እየተጠጣ ገበያተኛ ሁሉ ትዳራችሁ ሙሉ ይሁን፣ ያማረ ትዳር ይሁን፣ ውለዱ ክበዱ፣ ወንድ ውለዱ፣ ሴት ውለዱ፣ እያሉ ይመርቃሉ፡፡
እግረ መንገዳቸውን የማን ቤተሰብ ጥሩ ቀልቦ ሙሽራዋ እንዳማረባት፣ የማን ቤተሰብ እንዳጎሳቆለ፣ አለባበሷ፣ መዋቢያዋ ታይቶ፣ የእከሌ ቤተሰብ ጥሩ ይዟል፤ ሙሽራዋ አምሮባታል እያሉ ለቤተሰቡም ለባሏም ዕውቅና ይሰጣሉ።
ይህ ሥነ ሥርዓት ከተፈፀመ በኋላ ሙሽራዋ ከሕብረተሰቡ ጋር በይፋ የምትቀላቀል ሲሆን÷ የተለያዩ ማሕበራዊ ክዋኔዎችን ለመስራት ወደ አዲስ ምዕራፍ ትሸጋገራለች።
በማስተዋል አሰፋ