Fana: At a Speed of Life!

ሕዳሴ ግድብ አፍሪካውያን ያለምዕራቡ ዓለም ድጋፍ ፕሮጀክት መገንባት እንደሚችሉ አሳይቷል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካውያን ያለምዕራቡ ዓለም ድጋፍ ግዙፍ ፕሮጀክት መገንባት እንደሚችሉ ያሳይቷል።

ዘ ሳህል ሲግናል የተባለው  የዩቲዩብ ገጽ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ባወጣው ትንታኔ÷ ኢትዮጵያ የዓለም ዐይኖች ያተኮሩበትን የሕዳሴ ግድብ አጠናቅቃ ማስመረቋን አንስቷል፡፡

ሀገራት ግድቡን በተመለከተ ፊታቸውን አዙረውባት የነበረ ቢሆንም በጽናት ግድቡን ገንብታ ለፍጻሜ አብቅታለች ብሏል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አርሶ አደሮችም፣ የመንግስት ሰራተኞችን፣ ባለሀብቶችን ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ግድቡን በራስ ዓቅም ገንብታ ማጠናቀቋን ጠቅሷል፡፡

ግድቡ ሀይል ከማመንጨት በላይ ብዙ ትርጉም አለው ያለው ዘ ሳህል ሲግናል÷ የግድቡ መጠናቀቅ አፍሪካውያን ያለምዕራቡ ዓለም ድጋፍ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብተው ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ያሳየ ነው ብሏል፡፡

የሕዳሴ ግድብ ከግድብነት ባለፈ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ያፈረሰ፣ ሉዓላዊነትን ያረጋገጠ እና የአፍሪካውያንን ተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅም ከፍ ያደረገ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ግድቡ ለቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ እድገት ወሳኝ መሆኑን እና ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የተፈጥሮ ኃብታቸው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ መንገድ ከፍቷል ሲል አመላክቷል፡፡

ግድቡ የተረጋጋ የውሃ ፍሰት እንዲኖር እንደሚያደርግ በመጠቆም፤ በዚህም ሱዳን እና ግብፅ ለመስኖ፣ ለቤት ውስጥ እና ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውል ጤናማ ፍሰት ያለው ውሃ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብሏል፡፡

አፍሪካ ለማደግ እና የራሷን ሀብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ እንደማትጠይቅ በመጠቆም፣ የሕዳሴ ግድብ የአፍሪካውያንን የመልማት እድል ወደ ሌላ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.