የኢትዮጵያ አዳጊዎች ኦሊምፒክ በጥቅምት ወር ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሁለተኛው የኢትዮጵያ አዳጊዎች ኦሊምፒክ ጨዋታ በመጪው ጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ይደረጋል አለ፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በሰጡት መግለጫ÷ በውድድሩ እድሜያቸው ከ14 እስከ 17 ዓመት የሆኑ አዳጊዎች ይሳተፋሉ፡፡
የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ በአዳጊ ስፖርተኞች መካከል የኦሊምፒክ መንፈስን በማስረፅ ተሳትፏቸውን ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል።
በኦሊምፒክ ጨዋታው የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ስፖርተኞች በአንጎላ በሚካሄደው የአፍሪካ አዳጊዎች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።
ከጥቅምት 8 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው የኢሊምፒክ ጨዋታ ከ12 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚመረጡ አዳጊ ስፖርተኞች በ20 የስፖርት አይነቶች ይሳተፋሉ።
በወርቅነህ ጋሻሁን