የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የላቀ ሚና አላቸው አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ የሚያስችል የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ መላኩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ እድል ፈጥሯል።
የኢንዱስትሪ ምርታማነትን መጨመርና የአምራች ዘርፉን እድገት ማሳደግ የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር የሚያጠናክሩ የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አካታች የኢንዱስትሪ ልማት ተግባራዊ በመደረጉ ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
የኢንዱስትሪው የገበያ ድርሻ 30 በመቶ እንደነበር ጠቁመው ÷ በተከናወኑ የለውጥ ተግባራት ምጣኔውን ወደ 45 በመቶ ከፍ ማድረግ እንደተቻለ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዘርፉ የሚፈጠረውን የሥራ እድል በእጥፍ በመጨመር ያለውን ሚና ማጉላት መቻሉን ነው ያብራሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በትናንትናው ዕለት የተመረቀውና የኢነርጂ ምንጭ የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ለዘርፉ ማንሰራራት ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን አመልክተዋል።