Fana: At a Speed of Life!

በተለምዶ አጠራሩ ‘ሿሿ’ በሚል የሚታወቀውን የውንብድና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሚኒ ባስ ታክሲ በመጠቀም በተለምዶ አጠራሩ ‘ሿሿ’ በሚል የሚታወቀውን የውንብድና ወንጀል የፈጸሙ አራት ግለሰቦች ከ7 እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው፡፡

የቅጣት ውሳኔ የተወሰነባቸው ሰናይት ገ/እግዚአብሔር፣ ሄርሜላ ካሳ፣ መክሊት አዳነ እና ዳኛቸዉ መንግስቴ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 671 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት የፍትህ ሚኒስቴር የየካ ምድብ ዐቃቤ ሕግ በሕዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም በነበረ ችሎት ቀጠሮ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በክሱ ዝርዝር ላይ እንዳመላከተው፤ ተከሶሾቹ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸዉ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት ሲሆን በየካ ክ/ከ ወረዳ 07 ሌክስ ፕላዛ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ  የታክሲ አሽከርካሪ፣ ረዳት እና ተሳፋሪ በመምሰል 3 ግለሰቦችን ወደ ታክሲ ውስጥ እንዲገቡ ካደረጉ በኋላ አንገታቸውን በማነቅ እራሳቸውን እንዳይከላከሉ በማድረግ ሶስት ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ የወርቅ ሀብል፣ 5 ሺህ ጥሬ ብር እና ከአንድ የግል ተበዳይ ደግሞ በሞባይል ባንኪንግ ከ13 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ወስደው ከታክሲ እንዲወርዱ አድርገዋል።

ተከሳሾቹ በችሎት ተገኝተው ክሱ እንዲደርሳቸውና በንባብ እንዲረዱት የተደረገ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ በክሱ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በማስመዝገባቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ለችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመመርመር ተከሳሾቹ እንደየተሳትፎ ደረጃቸው በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በዚህም ሰናይት ገ/እግዛብሔር በ11 ዓመት፣ ሄርሜላ ካሳ በ7 ዓመት፣ መክሊት አዳነ በ9 ዓመት እንዲሁም ዳኛቸው መንግስቴ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.