ኢሬቻ የሀገርን ማንሰራራት የሚደግፍ የኦሮሞ ክብረ በዓል ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢሬቻ የሀገርን ማንሰራራት የሚደግፍ የኦሮሞ ክብረ በዓል ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በነገው ዕለት በሆረ ፊንፊኔ እንዲሁም በማግስቱ እሑድ በሆረ ሀርሰዴ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በመልዕክታቸው እንዳሉት፥ ኢሬቻ ህዝቡ የጨለማው ወቅት አልፎ የሚገናኝበት የብርሃን ጊዜ መድረሱን የሚያበስርበት እንዲሁም በአንድነት በመሰባሰብ አምላኩን የሚያመሰግንበት በዓል ነው፡፡
ያደጉ ሀገራት የእድገታቸው ምስጢር ለሀገር በቀል ፍልስፍና ትኩረት መስጠታቸው እንደሆነ ጠቅሰው፥ መንግስት የህዝቡን ነባር ባህላዊ እሴቶች በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ኢሬቻ በሀገር በቀል ፍልስፍና ላይ የተሞረኮዘ የኦሮሞ ህዝብ ክቡር በዓል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ኅብረትን የሚያጠናክር፣ አንድነትን የሚያፀና እንዲሁም የኦሮሞን ህዝብ ማንነት ከፍ አድርጎ የሚያሳይ በዓል መሆኑን አውስተዋል፡፡
በዓመቱ ውስጥ ለተገኙት ድሎችና ስኬቶች በማመስገን ለመጪውም መልካም እንዲሆን በባህሉ መሰረት ስኬት የሚሰበክበት ትልቅ በዓል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ኢሬቻ ከባህላዊ እሴት ያፈነገጡ ድርጊቶችን በመከልከልና ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለውን መስተጋብር በማጠናከር በፍቅር እንደሚከበር ነው ያስገነዘቡት፡፡
የዘንድሮው በዓል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተመርቆ ስራ በጀመረበት ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰው፥ በበዓሉ ላይ ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የኢሬቻን ሰላማዊነትና አቃፊነት ለዓለም በማሳወቅ በዓሉን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን እያጠናከረን የብልጽግና ጉዟችንን ለማሳካት እንሰራለን ብለዋል፡፡