ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደ ኢሬቻ ያሉ የኢትዮጵያን መልኮች ለዓለም ለማሳየት እየሰራ ነው – አቶ አድማሱ ዳምጠው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደ ኢሬቻ ያሉ የኢትዮጵያን መልኮች ለዓለም ለማሳየት እየሰራ ነው አሉ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያዘጋጀውን የኢሬቻ ኮንሰርት ባስጀመሩበት ወቅት፥ ኢሬቻ የፍቅር፣ የመቻቻልና የይቅር ባይነት በዓል መሆኑን አንስተዋል፡፡
አብሮ የመኖር፣ የእኩልነት፣ ጨለማው ዘመን ታልፎ መጭው ብርሃናማ ጊዜ የሚተካበትና ወቅቶችን ላሸጋገረ ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያን ለማብሰር በትጋት እየሰራ ይገኛል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ተቋሙ እንደ ኢሬቻ ያሉ የኢትዮጵያን መልኮች ለዓለም ለማሳየት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህቦችን ለዓለም ለማሳየትና ኢሬቻን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ እንዲተዋወቅ ሰፊ ሽፋን ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
ይሄን ልዩ ቀን ተመልካቾች የቴሌቪዥን ምርጫቸውን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በማድረግ የኢሬቻ ኮንሰርትን በቀጥታ እንዲከታተሉ ጋብዘዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ