Fana: At a Speed of Life!

አብሮነትንና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን እና ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር አንጻር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው አለ የሰላም ሚኒስቴር፡፡

14ኛ ዙር የወጣቶች “በጎነት ለአብሮነት” ስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በወሎ፣ ጅማና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ተካሂዷል።

የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አበበ ወርቁ በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት÷ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ሰላም ግንባታ ዙሪያ ማሰልጠን መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

ወጣቶቹ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካበቢ የተውጣጡ በመሆናቸው የራሳቸውን ባህል፣ ወግና እሴት ለሌሎች በማጋራት በልዩነት ውስጥ አንድነትን በማጎልበት ለሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ሰላምን ከማጠናከር፣ በሕዝቦች መካከል አብሮነትን ከማጎልበትና ብሔራዊ መግባባትን ከመገንባት አንጻር አበረታች ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ በሚኒስቴሩ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማሕበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም መሪ ሥራ አስፈጻሚ ገመቺሳ ኢቲቻ ÷ ወጣቱ በማህበራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎት መሪ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል ።

በተለይ ማሕብረሰቡን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በማገዝ ማሕበራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የማስተባበር ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በስንታየሁ አራጌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.