በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ የመስኖና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ንቅናቄ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ የበጋ መስኖና የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ በክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የመስኖ ልማትን በማቀናጀት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የመስኖና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ እነዚህን ስራዎች በንቅናቄ መጀመር አስፈላጊ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ በመስኖ መልማት የሚችል ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መኖሩን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ እስካሁን በመስኖ ማልማት የተቻለው ከ367 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በመስኖ መልማት የሚችለውን መሬት ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን ግብአትና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በዚህ ዓመት የክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ እቅድና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
በአበበ የሸዋልዑል