የኢትዮጵያ መልክ የሚያሳዩ የአደባባይ ሐውልቶች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናዋ ውስጥ የታሪክ ምዕራፎችን በአደባባይ ቆመው የሚያስመለክቱ፣ ታሪካዊ ክስተቶችን የሚያወሱ እንዲሁም የጀግኖችን ታሪክ የሚዘክሩ የተለያዩ ሐውልቶች ይገኛሉ።
በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን በ30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ ከሚያወሳው የ6 ኪሎ ሐውልት ጀምሮ እስከ ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ሐውልት፣ ከአጼ ቴዎድሮስ ሴባስቶፖል እስከ አጼ ምንሊክ ሐውልት የኢትዮጵያ ታሪክን ለአላፊ አግዳሚው ያስተጋባሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓለ ፈለገ ሰላም የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ሰዓሊ አገኘሁ አዳነ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ የአደባባይ ሐውልቶች ታሪኮቻችን፣ ቅርሶቻችን እንዲሁም የእኛ መልኮች ስለሆኑ በተለየ ሁኔታ መጠበቅ አለብን።
የአደባባይ ሐውልት ከሥነ ጥበብ ዘርፎች መካከል አንዱ እንደሆነ አንስተው÷ የሥነ ጥበብ ባሕል እና የዕይታዊ ጥበብ ባሕል በየደረጃው ስራ የሚፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።
በሥርዓተ ትምህርታችን ውስጥ ሥነ ጥበብ የማጣጣም ባሕል ማደግ አለበት በማለት ገልጸው÷ ይህም በዙሪያችን ያሉ ጥበቦች ምንነታቸውን በመረዳት እንድንጠብቃቸውና ዋጋ እንድንሰጣቸው ያደርጋል ብለዋል።
በአደባባይ ሐውልቶች ውስጥ ኢትዮጵያ አለች ያሉት ሰዓሊ አገኘሁ÷ ኢትዮጵያ በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ያሳለፈችውን ዓመታት ከሚያሳየው የፈረሰው የሌኒን ሐውልት ጀምሮ በተለያዩ ሐውልቶች ውስጥ ኢትዮጵያ አለች ሲሉም አስረድተዋል።
አሁን ላይ በዘርፉ የሙያተኞች ቁጥር እንደጨመረና በሙያ ብቃትም ረገድ ብቃት ያላቸው ከያኒያን መፈጠራቸውን አንስተው÷ ቀደምት የአደባባይ ሐውልቶች በውጪ ሀገር ሙያተኞች ሲሰሩ እንደነበርና በሂደት ኢትዮጵያዊያን ቀራጺያን እየተተኩ ብዙ የጥበብ ስራዎች መስራታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰርፀ ፍሬስብሃት በበኩላቸው÷ በአደባባይ ሐውልቶች ዙሪያ መድረኮችን በማመቻቸት ጥልቅ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በውይይቶችም የሚያከራክሩ ሐሳቦችን በመድፈርና በማንሳት ጥልቅ ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው÷ በዚህም ሰዎች ካነበቧቸውና ከሚያውቋቸው ሐሳቦች ላይ የሚያካፍሏቸውን ጉዳዮች እንደ ግብዓት መውሰድ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!