10ኛው የከተሞች ፎረም ከህዳር 6 እስከ 10 በሰመራ ሎጊያ ከተማ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 10ኛው የከተሞች ፎረም “የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ ይካሄዳል፡፡
ከህዳር 6 እስከ ህዳር 10 በሚካሄደው ፎረም ላይ ከ150 በላይ ከተሞችና ከ10 በላይ የንግድ ድርጅቶች እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት የተለያዩ ከተሞች ይሳተፋሉ፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ፎረሙን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ በኢትዮጵያ የከተሞች ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ፎረሙ ከተሞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በጋራ በማልማት እንዲበለጽጉ የሚያስችል ሲሆን፥ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ወንድማማችነትን በማጎልበት የስራ ባህልን እንደሚያሳድግ የገለጹት ሚኒስትሯ፥ ከተሞች ያላቸውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም አቅም የሚያንጸባርቁበት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን በ73 ከተሞች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፥ ለከተሞች መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡
ፎረሙ በከተሞች የኮሪደር ልማት ስራዎች ትልቅ ትምህርት የሚቀሰምበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
በግዛቸው ግርማዬ