ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነትና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከልነቷን ይበልጥ ያሰፋል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነትና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከልነቷን ይበልጥ ያሰፋል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር።
ኃላፊው በነገው ዕለት በአዲስ አበባ የሚካሄደውን 25ኛ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ወድድሩ ላለፉት በርካታ ዓመታት የከተማዋን ውበት በድምቀት ለዓለም ሲያስተዋውቅ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ሩጫው አሁንም ለአዲስ አበባ ቱሪዝም ተጨማሪ ድምቀትና መስህብ በመሆን ለማህበራዊ መስተጋብር መጠናከር፣ ለህዝቦች አንድነት፣ አብሮት እና የባህል ትስስር የላቀ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ መካሄዱ የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነትና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከልነቷን ይበልጥ የሚያሰፋ መሆኑንም አንስተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ምቹ የሆኑና የስፖርት ቱሪዝምን የሚጠናክሩ በርካታ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን ጠቅሰው÷ ይህንንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ከፍ ለማድረግ መሰል ዝግጅቶችን በትብብር አጠናክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በውድድሩ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ ታዋቂ አትሌቶች በአዲስ አበባ ከመዝናናት ጎን ለጎን የተሰሩ ሰፋፊ መሰረተልማቶችን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።