Fana: At a Speed of Life!

ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቆጣጠር አስገዳጅ መመሪያ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቆጣጠር የወጣው አስገዳጅ መመሪያ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል አሉ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስቴሩ ከደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር ባወጣው ስታንዳርድ መሰረት ተሽከርካሪዎች የሚለቁትን የጋዝ መጠን በተመለከተ ገደብ አስቀምጧል።

ይህ ህግ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ይህም በካይ ጋዝን ይቀንሳል ነው ያሉት።

በተለይ ያረጁ ተሽከርካሪዎች የበካይ ጋዝ ልቀታቸውን እንዲቀንሱ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ ይህን የማያደርጉ ከሆነ እንዳያሽከረክሩ ይታገዳሉ ብለዋል።

ያረጁ ተሽከርካሪዎቻቸውን ወደ ኤሌክትሪክ ወይም የተፈጥሮ ጋዝ መቀየር የሚችሉበት አማራጭ መኖሩንም አንስተዋል፡፡

መንግስት የነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን ዜሮ ማድረግ ሳይሆን የሚለቁትን ጋዝ ነው መገደብ የፈለገው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የሚለቁት የበካይ ጋዝ መጠን ከተቀመጠው ስታንዳርድ በልጦ ክልከላ እንዳይጣልባቸው ቴክኖሎጂውን መጠቀም ወይም ወደ ታዳሽ ኃይል መቀየር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የተሽከርካሪ ባለቤቶች ይህንን እንዲያስተካክሉ የተሰጣቸው እፎይታ ጊዜ በመጠናቀቁ መመሪያው ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት ርምጃ መውሰድ እንዲችሉ በደብዳቤ አሳውቀናል ነው ያሉት።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.