የፋና ላምሮት ምዕራፍ 21 ስድስተኛ ሳምንት ውድድር ነገም ቀጥሎ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተወዳዳሪዎች ጠንካራ ፉክክር ጋር የቀጠለው የፋና ላምሮት ምዕራፍ 21 ስድስተኛ ሳምንት የድምጻውያን ውድድር በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይካሄዳል፡፡
የበርካታ ባለተሰጥኦ ድምጻውያን መታያ የሆነው ፋና ላምሮት የምዕራፍ 21 ውድድር ለ13 ሳምንታት የሚካሄድ ሲሆን÷ በየሳምንቱ ዳኞች በሙያቸው፣ ተመልካቾች ደግሞ ባልተገደበ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ይዳኛሉ፡፡
የምድብ ሁለት ስድስት ተወዳዳሪዎች በነገው የስድስተኛ ሳምንት ውድድር ራሳቸው የመረጧቸውን ሁለት ሙዚቃዎች ከዛየን ባንድ ጋር ያቀርባሉ።
ዳኞች በእጣ የደረሷቸውን ሁለት ተወዳዳሪዎች አዘጋጅተው ለውድድሩ የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡
የፋና ላምሮት ውድድር ተወዳዳሪዎች በተለያዩ ሳምንታት በራሳቸው፣ በዳኞች እና በተመልካቾች የሙዚቃ ምርጫዎች ነው የሚፈተኑት፡፡
በምዕራፉ ለፍጻሜ ለሚያልፉ 4 ተወዳዳሪዎች የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፥ ከገንዘብ ሽልማቱ በተጨማሪ አራቱም የፍጻሜ ተፋላሚዎች ወደ 6ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በቀጥታ ያልፋሉ።
የፋና ላምሮት ውድድር ቅዳሜ ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ በፋና በሁለቱም የቴሌቭዥን ጣቢያዎች፣ በፋና ዩትዩብ፣ ፌስቡክና የቴሌግራም ገጾች እንዲሁም በ www.fanamc.com ለአድማጭ ተመልካቾች በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል፡፡
አድማጭ ተመልካቾች በውድድሩ እየተዝናኑ በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት የዕለቱን የተወዳዳሪዎች መለያ ኮድ በመላክ ድምጽ መስጠት ይችላሉ፡፡