ኢትዮጵያ አፍሪካ እንደምትችል ያሳየች ሀገር …
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አፍሪካ እንደምትችል ያሳየች ሀገር ናት አሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፡፡
የአፍሪካ የቀድሞ መሪዎች ልጆችና የልጅ ልጆች በተገኙበት ለአፍሪካውያን የነፃነት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ጥቁሮች ማሸነፍ እንደሚችሉ ማሳየቷን አስታውሰዋል።
አፍሪካዊያንን አንድ ያደረገው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሲመሰረት የጎላ ሚና መወጣቷን ጠቅሰዋል።
አሁን ደግሞ በራሷ አቅም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገንብታ በመጨረስ እና ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመወጠን አፍሪካ እንደምትችል ማሳየቷን ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአፍሪካ የቀድሞ መሪዎች ልጆችና የልጅ ልጆች በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እያከናወነ ባለው ስራ እና በመጣው ለውጥ ኢትዮጵያውያን ሊኮሩ ይገባል ብለዋል።
የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ለአፍሪካ እድገት ያስፈልጋታል በማለት ገልጸው÷ ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚህ ትልቅ ማሳያ በመሆን በለውጥ ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ የአፍሪካ የቀድሞ መሪዎች ልጆችና የልጅ ልጆች ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ታድመዋል።
በቅድስት አባተ