Fana: At a Speed of Life!

ኅብረ ብሔራዊነታችንን ለብሔራዊ ጥቅማችን ማዋል አለብን – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ኅብረ ብሔራዊነታችንን ለብሔራዊ ጥቅማችን ማዋል አለብን አሉ፡፡

20ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው “የኢትዮጵያውያን የምክክር ቀን” ሲምፖዚየም በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት የብዝኃ ማንነት፣ ባህልና እሴት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሕዝቦች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ሰርታለች፡፡

ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መጎናፀፋቸውን በማንሳት የዘንድሮው በዓል አስተናጋጅ የሆነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማንሰራራት ጉዞ ላይ ሆና የሚከበር በዓል መሆኑን ገልጸው፥ ኅብረ ብሔራዊነታችንን ለብሔራዊ ጥቅማችን ማዋል አለብን ነው ያሉት።

በዓሉ በአስተናጋጅ ክልሎች የልማት ስራዎች እንዲከናወኑና የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአጭር ጊዜ በሰባቱም ክላስተር ከተሞች የተከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ምስክር መሆናቸውን አመልክተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ በበኩላቸው፥ በዓሉ ዳግም የሀገራችንን ገፅታ በሁለንተናዊ መልኩ የምናስተዋውቅበት ነው ብለዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በሰለሞን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.