ኢትዮጵያ ውስጥ 55 ሚሊየን ሰዎች የቴሌብር ተጠቃሚ ሆነዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ 55 ሚሊየን ሰዎች የቴሌብር ተጠቃሚ ሆነዋል አሉ፡፡
ከእነዚህም ውስጥ 30 ሚሊየን ያህሉ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆን ችለዋል ነው ያሉት፡፡
ዘመኑን የሚመጥን ለውጥ ለማምጣት መማርና ማደግ ሳንችል እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ 1960ዎቹ ላይ ከቆምን ነገር ይበላሻል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው የዓለም አስተሳሰብ መቀየሩን ጠቅሰው፥ እያንዳንዱ ዜጋ ጥሩ አዕምሮ እንዳለው በማመን ከመደበቅ ይልቅ መተባበርን ካስቀደመ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁንጮ የቴክኖሎጂ ማዕከል መሆን እንደምትችል አመላክተዋል፡፡
ይህ እንዲሆን ደግሞ መማር ብቻም ሳይሆን ለተማሩት አስቻይ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አንዳንዶች ዲጂታል 2025 ሲጀመር ቅዠት ነው ሲሉ እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ላይ 55 ሚሊየን ሰዎች የቴሌ ብር ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ 5 ሚሊየን ኮደርስ እንፍጠር በማለት በተጀመረው ስራ 2 ሚሊየን ኮደርስ ማሳካታችን ተዓምር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት በመደመር እሳቤ ተባብረን ኢትዮጵያን ከድህነትና ችግር በማውጣት መልኳን እና ውበቷን መግለጥ አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በአቤል ነዋይ