Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ትራንስፖርቷን ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክና የጋዝ ተሽከርካሪዎች እቀየረች ነው

ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣው ዓመታዊ ወጪ ከ4 ቢሊየን እስከ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ ይህም ሀገሪቷ ከወጪ ንግድ በዓመት የምታገኘውን ጠቅላላ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚወስድ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና በህዝብ ትራንስፖርት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠር ብር ለነዳጅ ማረጋጊያ ድጎማ ይመድቧል።
ለምሳሌ አምና ብቻ ወደ 70 ቢሊዮን ብር ለዚሁ አገልግሎት ወጪ አውጥቷል፡፡
ይህንን የበጀት ጫና ለመቀነስ መንግሥት ደረጃ በደረጃ የነዳጅ ድጎማዎችን እያነሳ እና የሀገር ውስጥ የችርቻሮ ዋጋን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር እያስተካከለ ይገኛል።
ጫናውንም ለመቀለስ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ እና የሀገር ውስጥ የፈሳሽ ጋዝ አጠቃቀም እንዲስፋ እያበረታታ ይገኛል፡፡
ይህም የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገዛውን የነዳጅ ጥገኝነት ለማስቀረት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና አካባቢን ከአየር ንብረት ብክለት ለመታደግ ትልቅ እርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ ከነዳጅ ተሸከርካሪዎች ወደ ፈሳሽ ጋዝ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የምታደርገው ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሪን በማዳን ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ይቀንሳል፡፡
የኤሌክትሪክና የጋዝ ተሸከርካሪዎች የዕለት ተዕለት የጉዞና የጥገና ወጪ ከነዳጅ ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነው።
የትራንስፖርት ዘርፍ ሽግግሩ ሀገራችን ያላትን የታዳሽ ሃይል አቅርቦት በብቃት በመጠቀም፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ያግዛል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ንጹህና ጤናማ አየር እንዲኖር ያደርጋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በባትሪ የሚሠሩ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ካላት የኃይል አቅርቦት ጋር በቀላሉ የሚጣጣሙ ናቸው።
የፈሳሽ ጋዝ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ነዳጅን በጋዝ በመተካት የትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ እንደ መሸጋገሪያ ያገለግላሉ።
በአሁኑ ወቅት ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መብዛት ጎን ለጎን የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ ያለው ሥራ የሀገሪቱን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ጉዞ ለማፋጠን እጅግ ወሳኝ ነው።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ እየተሰራ እንዳለው ሁሉ፣ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማደያዎች ግንባታ እና አገልግሎትም እንዲሁ አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ሀገሪቱ በሶማሌ ክልል ካሉብ የምታመርተውን የሀገር ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ዘመናዊ የማደያ መሠረተ ልማቶችን እየገነባች ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ አውቶብሶችን ከነዳጅ ወደ ጋዝ ለመቀየር ባለው እቅድ መሠረት፣ በቃሊቲ የተገነባው የኢኤንጋዝ ብራንድ የፈሳሽ ጋዝ ማደያ ግንባታው ተጠናቆ ለስራ ዝግጁ ሆኗል።
ይህ ማደያ ግዙፍ የጋዝ ማከማቻ ታንኮች እና ተሸከርካሪዎችን በጋዝ የመሙያ መሳሪያዎች የተገጠሙለት ነው።
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ፣ አዳማ እና ድሬዳዋ ከተሞች የመጀመሪያው ዙር የፈሳሽ ጋዝ ማደያዎች የሚገነቡባቸው ቀዳሚ ስፍራዎች ተደርገው ተመርጠዋል።
መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ያሉትን ከ1,200 በላይ የናፍጣ የከተማ አውቶብሶች ሞተራቸውን ወደ ጋዝ (CNG/LNG) የመቀየር ሰፊ ስራ እየሰራ ሲሆን፣ እነዚህ አውቶብሶች ዋነኛ የማደያዎቹ ተጠቃሚዎች ናቸው።
አዲስ በወጣው የመንግሥት መመሪያ መሠረት ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ የደረቅና የፈሳሽ ጭነት ተሸከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ መፈቀዱ፣ የጋዝ ማደያዎችን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረው ይገኛል።
ተሸከርካሪዎች ናፍጣና ቤንዚንን ትተው ጋዝና ኤሌክትሪክ መጠቀም ሲጀምሩ የትራንስፖርት ወጪን ቢያንስ 50 በመቶ መቀነስ ያስችላሉ።
ኢትዮጵያ ይህንን መሠረተ ልማት እያሰፋች ባለችበት ወቅት፣ የግል ባለሀብቶችም በማደያ ግንባታ እና የጋዝ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ እንዲሳተፉ መንግሥት ጥሪ እያቀረበ ይገኛል።
በአጠቃላይ የነዳጅ ወጪ የኢትዮጵያ ትልቁ የውጭ ምንዛሪ ወጪ በመሆኑ፣ ይህንን ወጪ በሀገር ውስጥ ታዳሽ ኃይል መተካት ለሀገሪቱ ማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት ወሳኝ እርምጃ ነው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.