Fana: At a Speed of Life!

ከያኒው ከ34 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ እናት ሀገሩ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አንጋፋው ከያኒ ታምራት አበበ ከ34 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በአዲስ ራዕይና በናፍቆት ወደ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ መጥቷል።

ሙዚቃ በዜማና በግጥም ከቀረጹት ጥቂት የጥበብ መሀንዲሶች መካከል ስሙ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

የዜማና ግጥም ደራሲው ታምራት አበበ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ባዶ እጁን እንዳልሆነ ከፋና ፖድካስት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

አፍሪካዊያን በአንድነት እንዲቆሙና የራሳቸውን ጥንካሬ እንዲያውቁ በሙዚቃ ቋንቋ ስለ አፍሪካ አንድነት አዲስ ሙዚቃ ተሰርቷል ብሏል።

ከከያኒ ታምራት አበበ የፈጠራ ብቃት የመነጩ ዜማዎችና ግጥሞች የሀገሪቱን ታላላቅ ድምፃውያን ታሪክ ቀይረዋል።

ከበርካታ ድምፃውያን ውብ ግጥም እና ዜማ ጀርባ ያለው ከያኒው፤ ለራሱ ካዜማቸው ስራዎቹ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ አንጋፋ ድምጻውያን የዜማና የግጥም ምንጭ ሆኖ ለደመቁባቸው ስራዎች የጀርባ አጥንት ነው።

ከእነዚህም መካከል የአንጋፋው ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወደውና ሀገራዊ ኩራትን የሚሰብከው “የ13 ወር ፀጋ” የተሰኘው ድንቅ ስራ የታምራት አበበ የፈጠራ ውጤት ነው።

ለአንጋፋው ማህሙድ አህመድም ‘ተዉ ልመድ ገላዬ’ን ጨምሮ በርካታ ዜማዎችንና ግጥሞችን በመስጠት ለድንቅ ስራዎቹ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።

ቴዎድሮስ ታደሰ፣ አስቴር አወቀ እና ሐመልማል አባተ በኪነ-ጥበቡ ዓለም ደምቀው እንዲታዩና አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ካደረጓቸው ስራዎች ጀርባ የታምራት አበበ የረቀቀ ዜማ እና ግጥም ጉልህ ሚና ነበረው።

ሌሎች በርካታ ድምፃውያንም በታምራት አበበ የጥበብ ውጤቶች በህዝብ ዘንድ ለመወደድ በቅተዋል።

በቅድስት ዘውዱ

የዜማና የግጥም ደራሲነት ብቃቱ ዛሬም ድረስ ሳይደበዝዝ ትውልድ የሚሻገሩ ዜማዎችን የሰጠንና ዛሬም ድረስ ለጥበብ የሚተጋው ታምራት አበበ ከፋና ፖድካስት ጋር የነበረውን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡- https://youtu.be/2HDg2GOfVdw?si=-zxMuzWI1zhrVyVJ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.