የሀላባ ብሔረሰብ የቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ሲምፖዚዬም እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀላባ ብሔረሰብ የቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ሲምፖዚዬም በሀላባ ቁሊቶ ከተማ እየተካሄደ ነው ።
የሀላባ ብሔረሰብ አዲስ ዘመን መለወጫ ”ሴራ በዓል” ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ሲምፖዚዬም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የሀላባ ዞን ም/ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ መሀመድ አሚን ሀጂ መሀዲ በመንገሳ ወር የሚከበረውን ”የሴራ” የዘመን መለወጫ በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የብሔረሰቡን ቋንቋ ”ሀላቢሳን” የትምህርትና የሥራ ቋንቋ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝና ለዘመናት ተጠብቆ ለዛሬ የበቃውን የሀገር ሀብት ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሀላባ ተወካይ ነጃት ግርማ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትር ዴዔታዎች፣ የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሙሁዲን ሁሴንና ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡
የሴራ በዓል ቀደም ብሎ በአዲስ አበባና ሆሳዕና እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ሲከበር የቆየ ሲሆን ÷ በነገው ዕለትም በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በድምቀት የሚከበር ይሆናል።
በብርሃኑ በጋሻው