Fana: At a Speed of Life!

የጋራ ሀገራዊ ትርክት ግንባታ ከሐሳብ እስከ ተግባር…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በከፋፋይ ትርክቶችና በተዛቡ የታሪክ አረዳዶች ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች።

እነዚህ ለፖለቲካዊ ትርፍ ተብለው የተሰነዱ ትርክቶች በማህበራዊ ትስስራችን ላይ ጥልቅ ጠባሳ ጥለው በዜጎች መካከል የጥርጣሬና የጥላቻ መጋረጃ እንዲጋረድ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የዚህ ውጤት ደግሞ በቃላት ሊገለጽ የማይችል የሰው ህይወት መጥፋት፣ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል እና የሀገር ቅርስና ንብረት መውደም ሆኗል።

ከቁሳዊ ውድመቱ በላይ ግን “እኛ” እና “እነሱ” በሚል መርዛማ ክፍፍል የታነጸ ትውልድ መፈጠሩ ለሀገራዊ አንድነት ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ይህንን ስብራት ለመጠገንና ሀገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የለውጡ መንግሥት “የመደመር” ፍልስፍናን እንደ መሪ ዕሳቤ በመውሰድ የጋራ ሀገራዊ ትርክት ግንባታን በዋነኛ ተግባርነት ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የመደመር ፍልስፍና የሀገሪቱን ቀደምት የታሪክ እሴቶች ከዘመናዊ የዴሞክራሲ ግንባታ ጋር በማዋሃድ ካለፉት ስህተቶች እየተማርን ወደፊት እንድንራመድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ሲሆን÷ ሦስት ዋና ዋና ምሰሶ በሆኑ በሀገራዊ አንድነት፣ ዜጎች ክብር እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ላይ የተመሰረተ ነው።

የመደመር ትርክት ኢትዮጵያ የነጠላ ትርክት ውጤት አለመሆኗን በመቀበል ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት የሚያቅፍና አሰባሳቢ የሆነ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ያለመ ነው።

የመደመር መንግሥት የተዛቡ የታሪክ አረዳዶችን በኃይል ሳይሆን በመግባባትና በመመካከር መፍታት ይኖርብናል የሚል ፅኑ እምነት ያለው ሲሆን÷ ይህንንም በተግባር ለማሳየት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ተቋማዊ ርምጃዎችን ወስዷል።

ከነዚህም መካከል በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የተቋቋመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተጠቃሽ ነው።

ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ ስራዎችን በማከናወን ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባህልን እያዳበረ ይገኛል።

በተጨማሪም የጋራ ኩራትን የሚያንፀባርቁ የታሪክ ቅርሶችን ማደስና መገንባት ሌላው ትልቅ ስኬት ነው። የዓድዋ ድል መታሰቢያ በአዲስ አበባ እምብርት ላይ መገንባቱ ኢትዮጵያውያን በጋራ የፈጸሙትን ተጋድሎ የሚያስታውስና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት የሆነ ተግባር ነው።

የአንድነት ፓርክና ሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎችም ዜጎች ያለፈውን ታሪካቸውን በትክክል እንዲረዱና ለጋራ የወደፊት ጉዟቸው ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው።

የመደመር ዕሳቤን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ለማስረፅ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አራት መጻሕፍት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ለኢትዮጵያ ብልጽግና የሚሆን ዝርዝር ፍኖተ ካርታ ከማቅረባቸውም በላይ በየደረጃው ከሕብረተሰቡ ጋር ለሚደረጉ ውይይቶች እንደ መነሻ አገልግለዋል።

በዲፕሎማሲው ረገድም ኢትዮጵያ የተከተለችው ዜጋ ተኮር ፖሊሲና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በዜጎች ዘንድ “እንችላለን” የሚል ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ የጋራ ሀገራዊ ትርክቱን አጠናክሮታል።

እነዚህ ግዙፍ የኢኮኖሚና የመሠረተልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ብዝኃነት ከሀብት ጋር በማጣመር ሁሉም ዜጋ የሀገሪቱ ማንሰራራት አካል መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ስምምነት ለመፍጠር እየተሰራ ነው። የመንግሥት አወቃቀርን ዲጂታላይዝ በማድረግ ሙስናን የመቀነስ፣ በግብርና ምርታማነት የኑሮ ውድነትን የመቆጣጠርና በቱሪዝም ዘርፍ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስራዎችን የመፍጠር እቅድ ተይዟል።

የዚህ ሁሉ ጥረት ዓላማ ኢትዮጵያን ካለፈው የልዩነትና የጥል ትርክት አውጥቶ ወደ ጋራ የብልጽግናና የአንድነት ትርክት ማሸጋገር ነው።

ይህ ታሪካዊ ጉዞ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ትብብር የሚጠይቅ ሲሆን÷ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የክብር ማማ ለማድረስ ዝግጁ መሆን ደግሞ የትውልዱ የቤት ስራ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.