Fana: At a Speed of Life!

በውይይትና በዲፕሎማሲ ገበያ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ድርሻ እንዲኖራት እየተሰራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጦርነት ሳይሆን በውይይት እና በዲፕሎማሲ ገበያ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ድርሻ እንዲኖራት ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ዲፕሎማሲ እና የቀጣናዊ ትስስር ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ እንዳይለያይ የተጋመደ በትብብር እንዳይሰራ ደግሞ የብሔራዊ ጥቅም ችግሮች፣ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት እና ፉክክሮች ያሉበት ቀጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቀጣናው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ፣ የብዝሃ ቋንቋ እና ባህል ባለቤት መሆኑን ገልጸው÷ ነገር ግን አንዱ ለአንዱ ጋሻ ሲሆን ሌላኛው ጥይት አቀባይ በመሆኑ ተገቢውን ሰላም እና ዕድገት ማረጋገጥ እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡

ውጥረቶችን ለማርገብ እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስ÷ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ደህንነቷን ለማረጋገጥ የባህር በር ያስፈልገኛል በማለት ጥያቄ ማቅረቧን እና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችም እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ የቀይ ባህር ባለቤት እንደነበረች አስታወሰው÷ በጦርነት ሳይሆን በውይይት እና በዲፕሎማሲ ገበያ የቀይ ባህር ድርሻ እንዲኖራት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

5 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባሕር ከ20 ሚሊየን የማይበልጥ ህዝብ ባላቸው ሀገራት የተሸፈነ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ 130 ሚሊየን ሕዝብ ይዛ የቀይ ባህር ድርሻ እንደሌላት ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ ፍትሐዊ ካልሆነ በዓለም ላይ ፍትህ የለም ነው ያሉት፡፡

የባህር በር ጥያቄው እንዳይሳካ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን በመጠቆም÷ ኢትዮጵያን ጎድቶ ትርፋማ መሆን አይቻልም ሲሉ አስገንዝበዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.