Fana: At a Speed of Life!

በመደመራችን በርካታ ስኬት መጥቷል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመራችን፣ በመሰባሰባችን፣ ይቅር በመባባላችን በርካታ ስኬት መጥቷል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ የተደርገው ትልቁ ነገር በኃሳብ ሀገርን መምራት ነው ብለዋል።

በዚህም በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው፤ መንግሥት ሁሉም አካባቢ ያለውን ኃብት እንዲያይ እና እንዲያለማ ዕድል መስጠቱን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የመጡ የሀገር መሪዎች የተሰራውን ስራ ማድነቃቸውን አንስተው፤ ይህ ዕውን ሊሆን የቻለው ኃሳብን በማስቀደም በኃሳብ ሀገር በመመራቱ እንደሆነ አንስተዋል።

ለውጡ እንደመጣ ያጋጠሙ በርካታ ችግሮች በመደማመጥ መፍትሄ እያገኙ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያሉ ልዩ ልዩ ኃብቶችን መልማታቸውን ገልጸው፤ በአዲስ አበባ የታየው የልማት ውጤት በሁሉም አካባቢ እየተዳረሰ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህ ሁሉ ውጤት የመጣው በመደመራችን፣ በመሰባሰባችንና ይቅር በመባባላችን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከሁሉ የሚቀድመው ሰላም በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁላችንም አካባቢዎቻችንን ሰላም ካደረግን፣ ከተደማመጥን በኃሳብ የሚመራ መሪ አለን ብለዋል።

የተመረቀው ፋብሪካ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያስቀር፣ ለአካባቢው የስራ ዕድል የሚፈጥር እና በሌሎች መንገዶች ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ማሕበረሰቡ የፋብሪካውን ደህንነት ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ወለጋ ሰላም መሆኑን እና ትልቅ የልማት ተስፋ ያለው መሆኑን በዛሬው ጉብኝት መታየቱን ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.