Fana: At a Speed of Life!

የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም አላቸው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በተፈጥሮ የማዕድን ሀብት የታደሉ በመሆናቸው በዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም አላቸው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡

የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ ርምጃዎችን ወስዷል።

በለውጡ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፉ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም ለዘርፉ በተሰጠው አነስተኛ ትኩረት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የዘርፉ ተጠቃሚነት አነስተኛ እንደነበረ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘርፉ ላይ ኢኒሼቲቭ በመቅርጽ የግሉ ዘርፍ በማዕድን ልማት በስፋት እንዲሳተፍ በርካታ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በዚህም በተለይም ከወርቅ ጋር በተገናኘ ጥቃቅን እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ተሰማርተው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።

የክልሉን እምቅ የማዕድን አቅም በአግባቡ በመምራት ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ገልጸው፤ በተለይም የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በተፈጥሮ የማዕድን ሀብት የታደሉ በመሆናቸው በዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም አላቸው ብለዋል።

በመሆኑም በአካባቢው ሰላምን በማጽናትና የማህበረሰቡ ን አንድነት በማጠናከር ልማት እና ብልጽግናን እውን ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ለትላልቅ ፋብሪካዎች ግብዓት በማምረት የሚያቀርበው የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ፤ ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል።

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.