በአፍሪካ በሳይበር ወንጀል የተጠረጠሩ 651 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፉ ፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) በአፍሪካ የሳይበር ማጭበርበር ወንጀል በሚል የተጠረጠሩ 651 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡
ኢንተርፖል በኤክስ ገፁ እንዳስታወቀው÷ ’ኦፕሬሽን ሬድ ካርድ 2 ነጥብ 0’ ሲል በሰየመው ዘመቻ ነው በ16 የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የሳይበር ወንጀል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በፈጠሩት የወንጀል መረብ በኦንላይን ኢንቨሰትመንት፣ በሞባይል የገንዘብ ዝውውር እና የኦንላይን የብድር ማመልከቻዎችን ህጋዊ በማስመሰል 45 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ኪሳራ አድርሰዋል ተብሏል፡፡
ግለሰቦቹ ከመዘበሩት ገንዘብ ውስጥ ኢንተርፖል እስካሁን 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ማስመለሱን ገልጿል።
በሳይበር ወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች በተጨማሪ 2 ሺህ 341 የሳይበር ማጭበርበሪያ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች መያዛቸውን የገለጸው ኢንተርፖል፤ ተጠርጣሪዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ 1 ሺህ 442 በላይ ድህ ገፆችን መዝጋቱን ጠቁሟል።
ተጠርጣሪዎቹ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሀሰተኛ የኦንላይን ኢንቨስትመንቶችን በማቅረብ ሰዎች ገንዘብ እንዲያስገቡ ሲያደርጉ ነበር ብሏል።
እንዲሁም ሀሰተኛ የግለሰብ አካውንት በመክፈት በኦንላይን ኢንቨስትመንት ብዙ ትርፍ እንዳገኙ በማስመሰል ራሳቸው ምስክርነት በመስጠት ሰዎችን ሲያታልሉ ቆይተዋል ነው የተባለው፡፡
የተደራጀ የሳይበር ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የገለጸው ኢንተርፖል÷ የሳይበር አጭበርባሪዎችን መረብ ለመበጠስ እና ወንጀሉን ለመከላከል የጋራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አፅዕኖት ሰጥቷል፡፡
በሚኪያስ አየለ