አፍሪካ በጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት የምታነሳው ጥያቄ ፍትሃዊ ነው – የአዘርባጃን ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት የምታነሳው ጥያቄ ፍትሃዊ ነው የአዘርባጃን ፕሬዚዳንት ኢልሃም አሊዬቭ፡፡
4ኛው የሹሻ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ፎረም “የመገናኛ ብዙሃን ሚና ሰላምና መተማመንን ለመመለስ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዘርባጃን ሹሻ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በፎረሙ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የተባበሩት መንግሥታት አካታችና አሳታፊ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የምታነሳው ጥያቄ ፍትሃዊና ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ተጨማሪ አካላት በምክር ቤቱ ካልተካተቱ በግጭት አፈታትና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ እክል እየፈጠረ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
አዘርባጃን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
በፎረሙ ላይ ከ53 ሀገራት የተውጣጡ ከ160 በላይ ተሳታፊዎች፣ 30 የዜና ወኪሎች፣ 60 የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም 10 ዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት እየተካፈሉ ይገኛሉ።
በምስክር ስናፍቅ