የኔልሰን ማንዴላ የመታሰቢያ ሙዚየም ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የጸረ አፖርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በሰለጠኑበት ኮልፌ ፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ የተሰየመው የመታሰቢያ ሙዚየም ተመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴባ ሎሲ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
![]()
ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ፖሊስ ለአፍሪካ የነፃነት ትግል የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸው÷ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አባት የሆኑትን ኔልሰን ማንዴላ አሰልጥኗል ብለዋል።
ኔልሰን ማንዴላ የፀረ አፓርታይድ ትግልን ለመቀላቀል በፈረንጆቹ 1962 በኢትዮጵያ ለወራት ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውሰው÷ ይህም ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛችና የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ምልክት በመሆኗ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያውያን የፖሊስ አባላትና መኮንኖች መሰልጠናቸውን ጠቅሰው÷ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ እና ኮሎኔል ፈቃዱ ዋኬኔከአሰልጣኞች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ እውቀትና ልምዱን በማካፈል ለደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ገንቢ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።
መታሰቢያ ሙዚየሙ በኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን ወዳጅነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት የምታበረክተው አስተዋፅኦ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።