የፍቼ ጫምበላላ ዋዜማ “ፊጣራ” ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ብሔር ዘመን ፍቼ ጫምበላላ በዓል ዋዜማ “ፊጣራ” ሥነ ሥርዓት በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የክልሉ እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የሲዳማ ሕዝብ በአያንቱዎች እየተመራ በራሱ አቆጣጠር ዘመንን የሚለውጥበት የፍቼ ጫምበላላ በዓል በውስጡ ብዙ የሀገር አንድነትና የሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ እሴቶች አሉት፡፡
ሁሉም ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቅቆ የጫምበላላ በዓልን ይታደማል ፤ልጆች ይዝናናሉ፤ ከብቶችም ከቀዬ አይወጡም ወይም አይሰማሩም፤ በጊቢ ውስጥ የሚመገቡት ተዘጋጅቶላቸው ይቆያሉ።
በፊቼ ቀን እንኳን ሰው ዛፍም ክብር አለው፤ ዛፍ መቁረጥ የተከለከለ ነው፤ ሕጻናትን መግረዝም እንዲሁ፡፡
”የፊጣራ ምሽት” በሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምበላላ በዓል ላይ ከሚከወኑ ሁነቶች መካከል አንዱ ሥርዓት ነው ።
ፊጣራ ጫምበላላ ከመድረሱ በፊት ላለፉት አስራ አምስት ቀናት አባቶች በጾሞና ጸሎታ ያሳልፋሉ፤ ዛሬም ጾማቸውን የሚፈቱበት ቀን ነው።
በዚህ የጾም መፍቻ ሥርዓትም አባቶች በአንድ ሻፌታ (ቡርሳሜ የሚበላበት እቃ) ውስጥ ሁሉም በሕብረት ማዕድ ይቋደሳል፡፡
ይህም አዲሱ ዓመት አንድነት የሚጠናክርበት እና ሰላም የሚበዛበት እንዲሆን ለመመኘት የሚከናወን ሥርዓት ነው፡፡
ቡርሳሜ ሲበላ ወተት አብሮ ይቀርባል፤ ይህን ወተት ደግሞ አባቶች በአንድ መጠጫ አብረው ይጠጣሉ፡፡
መጠጫው ”ገሬሬ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን÷ በገሬሬ አብሮ የሚጠጣው አንድነት እና ፍቅርን ለማሳየት ነው። በዚህ ቀን የተጣላም እንኳን ቢኖር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ታርቆ አብሮ ማዕድ ይቋደሳል።
የፍቼ ጫምበላላ በዓል በነገው ዕለት ከማለዳው ጀምሮ በ”ሶሬሳ ጉዱማሌ” በአባቶች የቄጣላ ሥርዓት በድምቀት የሚከበር ይሆናል፡፡
በጥላሁን ይልማ